ኢንዱስትሪዎች ይበረታታሉ

Posted in Know How

አገራችን ኢትዮጵያ የያዘችውን ፈጣን የእድገት መስመር ቀጣይነት ለማረጋገጥና እቅዷን  ለማሳካት  የተለያዩ ስራዎች በመሰራት ላይ ይገኛሉ፡፡ የሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን  እቅድ ውስጥ ከተካተቱት   የማኒፋክቸሪንግ ዘርፎችን ለማሳካት በመንግስት ሙሉ በሙሉ ከተያዙ ፕሮጀክቶች ባለፈ የግሉን ዘርፍ ለማበረታታት በርካታ ድጋፎች በመንግስት በኩል ይደረጋሉ፡፡

የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣንም የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማበረታት ስርዓቶችን ዘርግቷል፡፡ ከነዚህም ውስጥ የቀላል የጉምሩክ ስነ-ስርዓት፣ የቀረጥ ማበረታቻ እንዲሁም የተመረጡ የኢኮኖሚ አንቀሳቃሾች ስርዓት ይገኙበታል፡፡

በማበረታቻ ስርዓቶቹ በዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዕቅዱ ላይ ለዕቅዱ መሳካት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው የኢንዱስትሪ ዘርፎች ተሰማርተው ምርቶችን ለውጪ ገበያ የሚያቀርቡ ቀላል የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናሉ፡፡ ይሁን እንጂ በሌሎች ዘርፎችም የተሰማሩ ቢሆንም ተጨማሪ እሴት የሚፈጥሩ እስከሆኑ ድረስ በተመሳሳይ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡

በዚህ መሠረት ቀላል የጉምሩክ ሥነ-ሥርዓት ተጠቃሚ የሚሆኑ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጉልህ ድርሻ የሚኖራቸው ልማታዊ ባለሀብቶችን ለመምረጥ የሚያስችል የየዘርፉን ባህሪይ ታሳቢ ያደረገ ግልፅ የመምረጫ መስፈርቶች ተዘጋጅተው ግብር ከፋዮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል፡፡  

በስርዓቶቹ፤ አምራቾች፣ ላኪዎች፣ በግብርና እና በኢንዱስትሪ የተሰማሩ የቀላል ጉምሩክ አፈጻጸም በመመሪያ የተቀመጡ መስፈርቶችን ማለትም ከስራ እድል ፈጠራ፣ የውጭ ምንዛሬ፣ አዲስ የገበያ መዳረሻ በመፍጠር፣ በአውቶሜሽን የታገዘ የመረጃ ስርዓት እንዲሁም የተለያየ የመመረጫ ነጥቦችን በሟሟላት የቀላል የጉምሩክ ስነ-ስርዓት ተጠቃሚ መሆን ይችላሉ፡፡

በቀላል የጉምሩክ ስነ-ስርዓት የተመዘገቡ ግብር ከፋዮች የሚያገኙት አገልግሎት         

በዝቅተኛ ሥጋት ደረጃ ተመድበው ፈጣን አገልግሎት የማግኘት፤

ከሰነድ ምርመራ እና ፍተሻ ጋር በተያያዘ እንደአስፈላጊነቱ የሚደረግ የጉምሩክ ቁጥጥር የቅድሚያ አገልግሎት የማግኘት፤

የፍተሻ አገልግሎት በራሱ በተጠቃሚው መጋዝን የማግኝት፤

በዝቅተኛ የቅድመ ዕቃ አወጣጥ የጉምሩክ ቁጥጥር እና ጣልቃ ገብነት የመስተናገድ፤

ቅድመ ዕቃ አወጣጥ (Prearrival clearance) የጉምሩክ ስነስርዓት መፈፀም ሥርዓት ተጠቃሚ መሆን፤

የሚያቀርቡት አቤቱታና ቅሬታ በቅድሚያ እንዲታይ የሚደረግበት ሁኔታ የማግኘት፤እና

ባቀረቡት ኢንቮይስ መሰረት እንዲስተናገዱ ማድረግ እና በቀጣይ በድህረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት እንደ አሰፈላጊነቱ የሚታይበት ሁኔታ እንዲመቻች ይደረጋል፡፡

ግዴታዎች

1.  በጉምሩክ ልዩ አገልግሎት ተጠቃሚነት ማረጋገጫ ሠርተፊኬት የተሰጠውን ልዩ መብት ያለ አግባብ ያለመጠቀም፤

2.  የገቢም ሆነ ወጪ ዕቃዎች ለፍተሻ ሲመረጡ ተባባሪ መሆን፤

3.  በድርጅታቸው ውስጥ የስነ ምግባር ችግር ያለባቸው ሰራተኞች እንደ ጥፋቱ መጠን እርምጃ የመውሰድ፤

4.  ድርጅቱ ለድህረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት ሲመረጥ የኦዲት ሂደቱ በአግባቡ ተፈጻሚ እንዲሆን አሰፈላጊው ሰነዶች በማቅረብ የሚጠየቁ መረጃዎችን በመስጠት እንዲሁም ምቹሁኔታ በመፍጠር ተባበሪ መሆን ፤

5.  በገቢ ግብር የሚፈለግባቸውን ክፍያ በወቅቱ የመክፈል፤

6.  ለባለስልጣኑ ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎች ሲጠየቁ ተገቢውን መረጃ የመስጠት፤

7.  በባለስልጣኑ ኦዲተሮች የሚሰጡ  የማስተካከያ ምክር መተግበር እና የአሰራር መሻሻያ ማድረግ፤

8.  በድርጅቱ ውስጥ የሰራር እና የቦታ ለውጥ ወዘተ ሲደርግ በወቅቱ ለባለስልጣን የማሣወቅ እና

9.  የሚገጥማቸው ችግር በየወቅቱ ሪፖርት ማድረግ እና ችግርችን በጋራ  ለመፍታት ዝግጁ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

በራሄል ወልዴ
Visitors: Yesterday 146 | This week 520 | This month 1516 | Total 435889

We have 462 guests and no members online