ደረሰኝ

Posted in Know How

 

    

ደረሠኝ በዕቃ ወይም በአገልግሎት ግብይት ላይ ተመስርቶ ከሻጩ/አቅራቢው/ ለገዥው የሚሠጥና ግብይት ስለመፈፀሙ ፣ ገንዘብ ስለመሰብሰቡ ፣ ዋጋው ስለመከፈሉ ወይም ለወደፊት ለመክፈል ውል መግባቱን የሚያሣይ ሰነድ ነው፡፡በገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 መሰረት ከደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች በስተቀር የደረጃ "ሀ" እና "ለ" ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ፣ አስፈላጊ መረጃዎችንና ደረሰኞችን የመያዝ ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡ በርግጥ የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች የሒሳብ መዝገብ እንዲይዙ በህግ ባይገደዱም በፍላጎታቸው መያዝ ይችላሉ፡፡ የደረጃ "ሀ" እና የደረጃ "ለ" ግብር ከፋዮች የንግድ ሥራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅት ግብይቱ በደረሰኝ እንዲደገፍ ያደርጋሉ፡፡

ደረሰኞችመያዝ የሚገባቸው ዝርዝር መረጃዎች

የሽያጭ ደረሰኝ ቢያንስ የሚከተሉት መሰረታዊ መረጃዎች ሊይዝ እንደሚገባ መመሪያው በአንቀጽ 7 ንዑስ አንቀጽ 2 ያስቀምጣል፡-

1.      የአቅራቢውሙሉ ስም፣ አድራሻና የተመዘገበ የንግድ ስም የታተመበት፤

2.      የአቅራቢው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስ ቁጥር እና ለታክስ የተመዘገበበት ቀን የታተመበት፤

3.      የደረሰኙ ተከታታይ ቁጥር የታተመበት፤

4.      የገዥው ሙሉ ስም፣ አድራሻና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፤

5.      የተጓጓዘው፣ የተሸጠው ዕቃ ወይም የተሰጠው አገልግሎት አይነትና መጠን፤

6.      ታክስ የሚከፈልበት ግብይት ላይ የሚፈለገውን የተጨማሪ እሴት ታክስ/ የተርን ኦቨር ታክስ መጠን፤

7.      በፊደልና በአሃዝ የተፃፈ ጠቅላላ የሽያጭ ወይም ግብይት ዋጋ፤

8.      ደረሰኙ የተሰጠበት ቀን፤

9.      ደረሰኙን ያዘጋጅው እና/ወይም ገንዘቡን የተቀበለው ሠራተኛ ሥምና ፊርማ፣

10.    የደረሰኝ አታሚው ድርጅት ስም፣ የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣ የታተመበት ቀንና የአታሚው የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ቁጥር፤

11.    ደረሰኙ እንዲታተም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የተፈቀደበትን ደብዳቤ ቁጥርና ቀን ናቸው፡፡

የደረሰኝ ተጠቃሚ  ግብር  ከፋይ  ምን  ምን  ሃላፊነነቶች  አሉበት?

በመመሪያው አንቀጽ 19 ላይ ማንኛውም በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዕውቅና ያለውን ደረሰኝ የሚጠቀም ግብር ከፋይ የሚከተሉት ሃላፊነቶች እንዳሉበት ተቀምጧል፡-

በባለስልጣኑፈቃድ እና ዕውቅና ያልተሰጣቸውን /ህገ - ወጥ/ ደረሰኞችን አለመጠቀም፤

ለአንድ ግብይት ጥቅም ላይ የዋለን ደረሰኝ ለሌላ ግብይት አለመጠቀም፤

በበራሪና ቀሪ ቅጠሎች ላይ የተለያየ መረጃ አለመመዝገብ፤

ግብይቱ ከተከናወነበት ሽያጭ ዋጋ የተለየ የገንዘብ መጠን በደረሰኙ ላይ አለማስፈር፤

የደረሰኝ ህትመት ከተፈቀደለት ግብር ከፋይ ውጪ ለሌላ ግብር ከፋይ ጥቅም ላይ እንዲውል አለማድረግ፤

ያለደረሰኝ ሽያጭ አለማከናወን፤

  ደረሰኝ ለሚጠይቁ ግዥ ፈፃሚዎች ሽያጭ አለመከልከል፤ለአንድ አይነት ተግባር የሚውል ተመሳሳይ ቁጥር ያለው ደረሰኝ በማሳተም ጥቅም ላይ አለማዋል፤

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህትመት ፈቃድ መስጠት ከመጀመሩ አስቀድሞ የታተሙ ደረሰኞች በባለስልጣኑ ሳይመዘገቡ ወይም እንዲቋረጡ ከተደረገበት ጊዜ በኋላ አለመጠቀም፤

በእያንዳንዱ የደረሰኝ ቅጠል /ቅጅ/ ላይ በመመሪያውአንቀጽ 7 የተመለከቱ መረጃዎችን አሟልተው የያዙ ደረሰኞችን መጠቀም፤

በራሪና ቀሪ ቅጠሎች ያለው ደረሰኝ ማሳተም፣ ደረሰኞችን በጥንቃቄ መያዝ እና ግብይት የተፈፀመባቸውን ደረሰኞች በጥንቃቄ መያዝ እና ግብይት የተፈፀመባቸውን ደረሰኞች በግብር/ታክስ ህጉ እስከተገለፀ ጊዜ ድረስ ይዞ መቆየት፣ ለሒሳብ ምርመራ ወይም ለግብር አወሳሰን እንዲቀርብ በሚጠየቅበት ጊዜ ማቅረብ፤

የደረሰኝ አጠቃቀም መከታተያ ሌጀሩን ለሁሉም በግልጽ በሚታየበት ቦታ መስቀል እና ትክክለኛ መረጃ አንዲይዝ ማድረግ፤

የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያው በተለያየምክንያት አገልግሎት መስጠት ሳይችል ሲቀር በባለስልጣኑ ፈቃድ እና እውቅና የታተመ የሽያጭ ደረሰኝ መስጠት፤

ግብይት ተከናውኖ ለግዥ ደረሰኝ አንደተሰጠ 2ኛውን ቅጂ ወዲያውኑ ለሒሳብ ክፍል ማስተላለፍ እና/ ወይም ከማመሳከሪያ ሰነዶች ጋር ማያያዝ እንዲሁም ከላይ ከተጠቀሱት ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ተግባራትን ማከናወን፤

ያሳተመውን ደረሰኝ በቅደም ተከተል መጠቀም፣ በስህተት ቅደም ተከተል ሳይጠብቅ ጥቅም ላይ ያዋለ እንደሆነ በግብር ከፋይነት በሚስተናገድበት የባለስልጣኑ ቅ/ጽ/ቤት ማሳወቅ፤

ደረሰኝ ያሳተመ ግብር ከፋይ በተለያየ አካባቢ ወይም በተለያየ የንግድ ዘርፍ ለሚጠቀምባቸው ደረሰኞች የደረሰኝ ቅደም ተከተል ተፈፃሚ የሚሆነውን ለየንግድ ቦታው ወይም ለዘርፉ የተከፋፈሉትን ደረሰኞች መሰረት ማድረግ አለበት፡፡

 

Visitors: Yesterday 107 | This week 732 | This month 1882 | Total 433261

We have 491 guests and no members online