የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ሊያውቋቸው የሚገቡ አራት ነጥቦች

Posted in Know How

በአገራችን የግብር አስተዳደር ሥርዓት ግብርከፋዮች እንደ ዓመታዊ የሽያጭ ገቢያቸው በሶስት ዋና ዋና መደቦች ይከፈላሉ፤በደረጃ“ሀ”፣“ለ” እና “ሐ”፡፡የደረጃ“ሀ” ግብር ከፋዮች(ድርጅቶች ወይም ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው አንድ ሚሊዮን ብር ወይም ከዚህ በላይ) ሲሆን የግብር ዓመቱን ግብር የሚያሳውቁት የግብር ዓመቱ ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት አራት ወራት (ከሐምሌ1 እስከ ጥቅምት30)ነው፡፡ የደረጃ“ለ” (ድርጅትን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢያቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በታችና ከአምስት መቶሺ ብር በላይ) ግብር ከፋዮች የግብር ዓመቱ ከተጠናቀቀበት ጊዜ ጀምሮ ባሉት ሁለትወራት(ከሐምሌ1 እስከ ጳጉሜን5/6)ሲሆን የደረጃ“ሐ” (ድርጅትን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢው እስከ ከአምስት መቶሺ ብር በታች)ግብር ከፋዮች ደግሞ ለአንድ ወር(ከሐምሌ1 እስከ30) ግብራቸውን አስታውቀው መክፈል ይኖርባቸዋል፡፡ይህ ቢሆንም የራሱን የሂሳብ አመት እንደ ግብር አመት እንዲጠቀም ፈቃድ ለተሰጠው ግለሰብና ድርጅት የሂሳብ ዓመት ነው የሚባለው የግብር ከፋዩ ዓመታዊ የፋይናንስ ሂሳብ ሚዛን በሚዘጋበት ጊዜ የሚጠናቀቀው የአስራ ሁለት ወራት ጊዜ ነው፡፡

የ2010 ዓ.ም. የደረጃ“ለ” እና የደረጃ “ሐ” የግብር አከፋፈል መረጃ እንዳሳየን አብዛኛው ግብር ከፋዮች የመጡት በመጨረሻዎች የግብር መክፈያ ቀናት ነበር፡፡ይህ ደግሞ በአጭር ጊዜ ተስተናግደው መሄድ በሚገባቸው ጉዳይ ለረጅም ሰልፍና ወረፋ ከማጋለጥ ባለፈ አገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና ፈጥሯል፡፡ይህ ችግር እና መሰል መሰናክሎች የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች እንዳያጋጥሟቸው በገቢ ግብር አዋጅ፣ በታክስ አስተዳደር አዋጅ እና በዓለም አቀፍ የሂሳብ አያያዝ መርህ መሰረት የሂሳብ መዝገብ ከደጋፊ ሰነዶቻቸው ጋር ሂሳባቸውን ሲያሳውቁ ሊያውቋቸው የሚገቡ አራት ተግባራት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1.  መያዝ ያለባቸውን መዝገብ ማወቅ

የንግድስራ ገቢ ግብር የመክፈል ኃላፊነት ያለባቸው የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች በፋይናንስ ሪፖርት አቀራረብ ደረጃዎች መሰረት የተዘጋጁ የሂሳብ መዝገቦችን የመያዝ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን የሂሳብ መዝገቡ የሚከተሉትን ማካተት አለበት፡፡

ቋሚሃብቶች የተገዙበትን ወይም የተገነቡበትን ቀንና የሃብቶቹን ዋጋ፣

ሃብቱንለማሻሻል ያወጣውን ወጪና የሃብቱን የተጣራ የመዝገብ ዋጋ፣

የንግድስራውን ሃብትና ዕዳ የሚያሳይ መዝገብ፣

ከንግድስራ ጋር በተያያዘ በየቀኑ የተገኘውን ማናቸውንም ገቢና ወጪ የሚያሳይ ሰነድ፣

የዕቃ(የአገልግሎት) ግዥና ሽያጭን በተመለከተ፣

የንግድ ዕቃዎችንና አገልግሎቶችን ዝርዝር፣

የዕቃናየአገልግሎት ገዢዎችን እና አቅራቢዎችን ስምና የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር፣

የአቅራቢውን(የሻጩን) የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር የያዙ ቁጥር የተሰጣቸው ደረሰኞች፣

በግብርዓመቱ መጨረሻ በግብር ከፋዩ እጅ የሚገኙ የንግድ ዕቃዎች  ዓይነት፣ መጠንናዋጋ እንዲሁም የዋጋ መተመኛ ዘዴውን የሚያሳይ ሰነድ፣

የግብርከፋዩን የግብር ኃላፊነት ለመወሰን የሚያስችል ሌላ ማንኛውም ሰነድ፡፡

2.  ተቀናሽ የሚደረጉ ወጪዎችን ማወቅ

ግብር የሚከፈልበትን ገቢ ለመወሰን የሚከተሉት ከጠቅላላ ገቢ ላይ ይቀነሳሉ፡፡

በንግድ ስራ ገቢው ውስጥ የተካተቱትን ገቢዎች ለማግኘት፣ ለንግዱ ስራ ዋስትና ለመስጠትና የንግድ ስራውን ለማስቀጠል በግብር ከፋዩ በግብር ዓመቱ የተደረጉ አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎች፣

በግብር ዓመቱ ለተሸጠ የንግድ ዕቃ የወጣ ወጪ፣

በንግድ ስራው ላይ ሲውሉ ዋጋቸው የሚቀንስ የንግድ ስራ ሃብቶችና ግዙፋዊ ህልወት ለሌላቸው የንግድ ስራ ሃብቶች በግብር ዓመቱ የሚታሰበው ጠቅላላ የእርጅና ቅናሽ፣

የንግድ ዕቃን ሳይጨምር ግብር ከፋዩ በዓመቱ ውስጥ የንግድ ስራ ሃብትን በማስተላለፍ የገጠመው ኪሣራ፣

በተቀናሽነት የተፈቀዱ ሌሎች ወጪዎች፡-

የወለድ ወጪ፣

ለበጎአድራጎት ዓላማ የተደረገ ስጦታ (ለኢትዮጵያ የበጎ አድራጎትድርጅት ወይም የኢትዮጵያ ማኅበርወይም መንግሥት ባደረገው ጥሪ መሠረት ለልማት፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ለማስከበር፣ ሰው ሰራሽ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ወይም ወረርሽኝ ለመከላከል ወይም ለተመሳሳይ ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት የተደረገ ስጦታ ተቀናሽ ይደረጋል)፡፡ የሚፈቀደው ጠቅላላ የስጦታ ተቀናሸ ከግብር ከፋዩ ግብር የሚከፈልበት የግብር ዓመቱ ገቢ አሥር በመቶ የበለጠ አይሆንም፣

የማይሰበሰብ ዕዳ፣

ኪሳራ፣

ለሠራተኞች የተደረገ የህክምና ወጪ፣

የንግድሥራ ማስታወቂያ ወጪ፣

የተከራየውን የንግድ ሥራ ሀብት በራሱ ወጪ  የሚያድስ፣ የሚጠግን ወይም የሚያሻሽል ተከራይ፣

በካፒታል ዕቃዎች ኪራይ ውል መሰረት ለተያዘ የንግድ ሥራ ሀብት የሚፈቀድ ተቀናሽ፣

የዋና መሥሪያ ቤት ወጪ፡፡

3.  የእርጅና ቅናሽ ስሌትና አሠራር ማወቅ

ግብርከፋዩ ገቢውን ለማስገኘት በግብር ዓመቱ ጥቅም ላይ ላዋላቸው እና ዋጋቸው ለሚቀንስ ሀብቶች እና ግዙፋዊ ሀልዎት ለሌላቸው የንግድ ሥራ ሀብቶች ዋጋቸው በቀነሰው የገንዘብ መጠን ልክ የእርጅና ቅናሽ ለማድረግ ይፈቀድለታል፡፡

“ግዙፋዊ ሀልዎት የሌላቸው የንግድ ሥራ ሃብቶች” ማለት የሚከተሉት ናቸው ፡-

  የቅጅ መብት፣ ፓተንት፣ ዲዛይን ወይም ሞዴል፣ ፕላን፣ ምስጢራዊ ቀመር ወይም የአሠራር ሂደት፣ የንግድ ምልክት ወይም ለተወሰነ ዘመን ብቻ የሚያገለግል ሌላ ተመሳሳይ ሀብት፤

  የደንበኞች ዝርዝር፣ የሥርጭት መስመር ወይም የተለየ ስም፣ ምልክት ወይም ስዕል ወይም ለተወሰነ ዘመን ብቻ የሚያገለግል ሌላ ግዙፋዊ ሀልዎት የሌለው የንግድ ዘይቤ፤

ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖ ለተወሰነ ጊዜ የሚያገለግል ከውል የሚመነጭ መብት (ወጪው አስቀድሞ የተከፈለንም ጨምሮ)፤

ማንኛውንም ግዙፋዊ ሀልዎት ያለውን የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ሀብት ለማግኘት የወጣን ወጪ ሳይጨምር፣ ከአንድ ዓመት በላይ ጥቅም የሚሰጥ ወጪ፤

4.  ተቀናሽ የማይደረጉ ወጪዎችና ኪሣራዎች ማወቅ

የሚከተሉት ተቀናሽ አይደረጉም፡፡

  የእርጅና ተቀናሽ የሚደረግባቸው የካፒታል ወጪዎች፣

  የኩባንያ አክሲዮን ወይም የሽርክና ማህበር መሠረት የሆነውን ካፒታል ለማሳደግ የሚወጣ ወጪ፣

  ከ15% በላይ የሆነ በቀጣሪው የሚከፈል የጡረታ ወይም የፕሮቪደንት ፈንድ መዋጮ፣

  የአክሲዮን ወይም የትርፍ ድርሻ፣

  በካሳ መልክ የተመለሰ ወይም ሊመለስ የሚችል ወጪ ወይም ኪሣራ፣

  ህግን ወይም የውል ግዴታን በመጣስ የሚጣል የገንዘብ ቅጣት ወይም የሚከፈል ኪሣራ፣

  ለወደፊት ወጪዎች ወይም ኪሣራዎች መጠባበቂያ የተያዙ ሂሳቦችን፣ (ሆኖም ግን የፋይናንስ ተቋማትና የኢንሹራንስ ኩባንዎች ለመጠባበቂያ የሚይዙት ወጪ በተቀናሽ ይያዛል)፣

  የገቢ ግብር ወይም ተመላሽ የሚደረግ ተጨማሪ እሴት ታክስ፣

  መስሪያ ቤቱን ለመወከል ለተቀጣሪ የሚከፈል ከመቀጠር ከሚያገኘው ገቢ ከ10% በላይ የሆነ የውክልና ወጪ፤ (“የውክልና ወጪ” ማለት የግብር ከፋዩ ሠራተኛ የንግድ ሥራውን ለማስተዋወቅ እና ለማሳደግ እንግዶችን ከንግድ ሥራ ቦታው ውጪ ለመቀበል የሚያወጣው  የመስተንግዶ ወጪ ነው፡፡)

  ከሚከተሉት በስተቀር ለመዝናኛየሚወጣ ወጪ፣

     የግብር ከፋዩ የንግድ ስራ የመዝናኛ አገልግሎት መስጠት ከሆነ ወይም

     ሚኒስቴሩ በሚያወጣው መመሪያ በሚወስነው ልክ በማኑፋክቸሪንግ፣ በማዕድንና በግብርና ስራ የተሰማራ ቀጣሪ እንዲሁም የምግብ አገልግሎት 

የሚያቀርብ ተቋም ለሰራተኞቹ መዝናኛ የከፈለው ወጪ፡፡

ተቀናሽ እንዲደረግ ከተፈቀደው ውጪ የሚደረግ ስጦታ ወይም እርዳታ፣

የግብር ከፋዩ የግል ወጪ፣

የንግድ ስራ ሃብትን ግንኙነት ላለው ሰው በማስተላለፍ የሚያጋጥም ኪሣራ፣

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተቀናሽ አይደረጉም በማለት በደንብ የሚወስናቸው ወጪዎች፡፡

ግብር በህግ መሰረት ከህብረተሰቡ የሚሰበሰብ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ መንግስት የወጭ ፍላጎትን ለማሟላት ማለትም የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት፣ የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለማስፈን፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እና በጤና ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ማህበራዊ ጠቀሜታ የሌላቸውን ምርቶች ለመገደብ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡ አሁን በምንገኝበት የግሎባላይዜሽን ዘመን የታክስ ሥርዓቱ አላማ መንግስታዊ ተግባራት ለማከናወን የሚያስፈልገውን ገቢ ማስገኘት ብቻ ሳይሆን የተመጣጠነ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር ማድረግ እንዲሁም ከአገራት ጋር የሚኖረውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለማጠናከር ዋና መዘውር ሆኖ ያገለግላል፡፡ ስለዚህ የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች ከላይ በተዘረዘሩት አራት ነጥቦች መሰረት የሀገር ህልውና የሆነውን ግብርን በተሻለ አመለካከትና ግንዛቤ በመክፈልና ቸልተኝነትን ለማስቀረት ጠቃሚ ናቸውና ተግባራዊ ይደረጉ፡፡

በሰሎሞን ደግአረገ

 

Visitors: Yesterday 107 | This week 732 | This month 1882 | Total 433261

We have 483 guests and no members online