ጥቂት ስለ ኦዲት አይነቶች

Posted in Know How

 

የግብር ስርዓቱ ግብር ከፋይን በማመን ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ግብር ከፋዩ የሂሳብ መዝገቡን ራሱ ይዞና አስልቶ መክፈል የሚገባውን ግብር በራሱ እንዲያሳውቅ የሚፈቅድ ነው፡፡ ኦዲት  ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ በግብር ህጉ መሰረት በወቅቱ ገቢውን አሳውቆ መክፈሉን በማረጋገጥ የሚጠበቅባቸውን ግብር እና ታክስ ያልከፈሉትን ተጠያቂ የሚያደርግ ከመሆኑ ባሻገር ኪሳራን በማረጋገጥ እንዲሸጋገር፣ ተመላሽ ላላቸው ግብር ከፋዮች ተረጋግጦ ተመላሽ እንዲከፈል እና ግብር እና ታክሳቸውን በደበቁ ወይም አሳንሰው ባሳወቁት ላይ ያልተከፈለውን የግብር እዳ ከነወለድና ቅጣቱ እንዲከፈል የሚያደርግ ነው፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ስጋትን መሰረት አድርጎ በየጊዜው ሶስት አይነት ኦዲቶችን ያካሂዳል፡፡

የመጀመሪያው የድህረ እቃ አወጣጥ ኦዲት ሲሆን በገቢና ወጪ እቃዎች ላይ ግብር በትክክል መከፈሉን ለማረጋገጥ የጉምሩክ አገልግሎት አሰጣጥ የስጋት ስራ አመራር መስርቶ በመካከለኛ እና ዝቅተኛ የስጋት ደረጃ የተመደቡ ዕቃዎችን ያለ አካላዊ ፍተሻ እንዲለቀቅ ከተደረገ በኋላ በቀረበው ሰነድ ላይ ተመርኩዞ የሚሰራ የኦዲት አይነት ነው፡፡ ሁለተኛው፤ ታክስ ኦዲት ሲሆን የግብረ ከፋዮችን ማህደርና የሂሳብ ሰነዶች በመርመር የግብር ከፋዮችን የኋላ ታሪክ፣ የአከፋፈል ስርዓት፣ እውቀትና ክህሎት፣ ግብር ሲከፍሉ የሚያጋጥማቸው ችግር ወ..ዘ.ተ በማየት ታክሱ እንዲከፈል ድጋፍ ማድረግ በተጨማሪ ግብር ላለመክፈል የሚደረጉ ጥረቶች ካሉ በማስተማርና በመደገፍ ለአብዛኛው ግብር ከፋይ የመደገፍ ስራ የሚሰራ በሀገር ውስጥ ታክስ ላይ የሚከወን ነው፡፡ ሶስተኛው፤ ኢንቨስቲጌሽን ኦዲት ሲሆን ባህሪው ከታክስ ኦዲት ጋር ተመሳሳይ  ቢሆንም ከጉምሩክና ከሀገር ውስጥ ታክስ ጋር የተያያዙ ማንኛውም ጉዳዮች የሚመለከት ሲሆን ጥፋት ይኖርባቸዋል፣ ግብራቸውን በአግባቡ እየከፈሉ አይደለም፣ ግብር አጭበርብረዋል፤ ሰውረዋል ተብለው በሚጠረጠሩ ግብር ከፋዮች ላይ የሚካሄድ ኦዲት ነው፡፡ የዚህ አይነቱ ኦዲት የታክስ ውሳኔ እንዲሰጥ ከማስቻሉም በተጨማሪ የተፈጸመ ማጭበርበር በዝርዝር ምርመራ ማጣራት ለሚመለከተው የህግ አካል አቅርቦ በወንጀል እንዲቀጡ ያደርጋል፡፡ #በራሔልወልዴ

 

Visitors: Yesterday 113 | This week 114 | This month 1290 | Total 448649

We have 423 guests and no members online