ቅድመ ታክስ ክፍያ /Withholding/

Posted in Know How

አብዛኛውን ጊዜ እንደ አንድ የታክስ አይነት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ሆኖም ዊዝሆልዲንግ ታክስ ማለት አንድ ግብር ከፋይ ሊያገኝ የሚችለውን ገቢ መሠረት በማድረግ የግብር ሰብሳቢው ባለሥልጣን ከገቢ ማስታወቂያ ጊዜ አስቀድሞ ግብር የሚሰበስብበትሥርአት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ዊዝሆልዲንግ ወይንም ከክፍያ ላይ የሚሰበሰብ ቅድመ ታክስ እየተባለ ይጠራል፡፡ ዊዝሆልዲንግ በግዢና ሽያጭ ወይም የአገልግሎት ክፍያ በሚፈፀምበት ወቀትም ተሰልቶ ተከፋይ የሚሆንበት ሁኔታ አለ፡፡ ዊዝሆልዲንግ ገቢ በማግኘት የታክስ ግዴታቸውን ሳይወጡ የሚሰወሩትን በቀላሉ አነስተኛውን ምጣኔ እንዲከፍሉ ለማድረግ ስለሚያሰችል ለግብር አሰባሰቡ የመቆጣጠሪያ ዘዴ (Controlling mechanism) ነው፡፡

ቅድመ ታክስ በሁለት መልኩ ይከናወናል፡­

1. ወደአገር ውስጥ ለሚገቡ እቃዎች በሚከፈል የመድህን አረቦን (Insurance Premium) እና የመጓጓዣ ወጪ(Fright) ላይ ታስቦ አስመጪው 3 በመቶ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ ይህ ክፍያ ግብር ከፋዩ ለዓመቱ መክፈል ከሚኖርበት ግብር ይታሰብለታል፡፡ በዊዝሆልዲንግ የከፈለው በልጦ ከተገኘ ትርፉ ክፍያ በተረጋገጠ በዘጠና ቀናት ውስጥ ለግብር ከፋዩ ተመላሽ ይደረግለታል፡፡ በዘጠና ቀናት ውስጥ ካልተመለሰለት ባለፈው ሩብ ዓመት በንግድ ባንኮች ስራ ላይ በዋለው በከፍተኛው የማበደሪያ ልክ ላይ 25% ተጨምሮበት ወለድ ይከፈለዋል፡፡

2. በአንድ ጊዜ ግዥ ወይም በአንድ የእቃ አቅርቦት ከብር 10,000 በላይ ለሆነ ክፍያ ወይም በተለያዩ አገልግሎቶች በአንድ ጊዜ ግዥ ወይም በአንድ አገልግሎት ውል ከብር 500 በላይ ከሚፈፀም ክፍያ ላይ 2% ዊዝሆልድ ይደረጋል፡፡ ይህ ተቀናሽ ተደርጎ የሚያዘው በዊዝሆልዲንግ ኤጀንቶች ነው፡፡ ዊዝሆልድ የተደረገው መጠን ግብር ከፋዩ በዓመት ከሚከፍለው የበለጠ እንደ ሆነ በቁጥር አንድ በተገለፀው መልኩ ይፈፀማል፡፡ ከሚከፈላቸው ክፍያ ላይ 2 በመቶ ዊዝሆልድ የሚደረግባቸው የግብር ከፋይ መለያ ቁጥር ማቅረብ ለሚችሉ ሲሆን ማቅረብ የማይችሉ ከሆነ ግን 30 በመቶ ዊዝሆልድ ይደረግባቸዋል፡፡

የዊዝሆልዲንግ መጣኔ፡­-

1.   ከውጪ በሚገቡ እቃዎች ላይ 3 በመቶ

2.   ከ10 ሺህ ብር በላይ ግዢ/ሽያጭ ወይም ከ500 ብር በላይ የአገልግሎት ክፍያ ሲከናወን 2 በመቶ

የዊዝሆልዲንግ ወኪሎች እነማን ናቸው?

ከአንድ ግብር ከፋይ ላይ ቅድመ ታክስ /ዊዝሆልድ/ የሚሰበስቡና ህጉ የሚፈቅድላቸው ዊዝሆልዲንግ ኤጀንቶች /ወኪሎች/ ይባላሉ፡፡ከእነዚህ መካከል ከ600 ብር በላይ ወርሃዊ ደመወዝ በመክፈል ሰራተኛ ቀጥረው የሚያሰሩ ማናቸውም የመንግስትና የግልድርጅቶች/ቀጣሪዎች/፣ ሀላፊነታቸው የተወሰነ የግል ኩባንያዎች፣ የሽርክናድርጅቶች፣ ለትርፍ ያልተቋቋሙ የግል ድርጅቶችና ማህበራት ወዘተ የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ ከላይ በተገለፀው መሠረት ለዕቃዎችና አገልግሎቶች ከሚፈፀም ክፍያ ላይ ግብር ቀንሶ ገቢ ማድረግ ያለበት፣ /የዊዝሆልዲንግኤጀንት/ የሚከተሉት ግዴታዎች ይኖሩበታል፡­

ግብር ለተቀነሰበት ሰው ተከታታይ ቁጥር ያለው ህጋዊ ደረሰኝ ይሰጣል፣

ክፍያ የተፈፀመበትን የእያንዳንዱን ሰው ስም እና የስራ አድራሻ፣ ግብር ከፋይ መለያ ቁጥሩን / የተሰጠከሆነ/፣ በወሩ ውስጥ ለተጠቀሰው ሰው የተከፈለውን ገንዘብ አጠቃላይ ድምር፣ ተቀናሽ የተደረገውን ግብር ልክ ከግብር አስገቢ ባለስልጣን በሚሰጠው ቅፅ በወሩ ሞልቶ ያቀርባል፡፡

ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ቀንሶ /ዊዝሆልድአድርጎ/ ገቢ ያለማድረግ አስተዳደራዊ መቀጫ ያስከትላል

ቀንሶ ገቢ ያላደረገ ሰው ለእያንዳንዱ ተገቢውን ግብር ቀንሶ ለመንግሥት ገቢ ማድረግ ያለበት ሰው ወይም ድርጅት /የዊዝሆልዲንግ ኤጀንት/ ገቢ ሳያደርግ ለፈፀመው ለእያንዳንዱ ክፍያ ብር 1,000 መቀጫ ይከፍላል፣

ወኪሉ ከተከፋይ ሂሳብ ላይ ግብር ቀንሶ ገቢ የማድረጉን ስርዓት የመከታተል ወይም የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት ሆኖ ክትትሉን ወይም ቁጥጥሩን በተገቢው መንገድ ባለማከናወኑ ግብሩ ተቀንሶ ገቢ ላለመደረጉ ምክንያት የሆነ የሂሳብ ኃላፊ ወይም ማንኛውም ሌላ ኃላፊ ብር 1,000 መቀጫ ይከፍላል፡፡

Visitors: Yesterday 6 | This week 0 | This month 2202 | Total 824985

We have 332 guests and no members online