ግብር አወሳሰን፣ አሰባሰብና ምርመራ

Posted in Know How

         

የግብር አወሳሰን /Tax assessment/ ግብር ከፋዩ ያመነበትን ሂሳብ (ዓመታዊም ሆነ ወርሃዊ ታክሶች) ወስኖ በንግድ እንቅስቃሴው ያመነበትን የማቅረብ /Self Assessment/ ሂደት ሲሆን የታክስ ባለስልጣኑ ግብር ከፋዩ ያሳወቀውን /Self Assessment/ መሰረት በማድረግ /Official assessement/ ኦዲት በመስራት የሚያሳውቅበት ሂደት ነው። የግብር አወሳሰን ዘዴዎች ሁለት ናቸው፡፡

እነርሱም፡­

ሀ/ በሂሳብ መዝገብ ሰነዶች፣

ለ/ በግምት

. በሂሳብ መዝገብ መሠረት የሚደረግ ውሳኔ

ግብር በሂሳብ መዝገብና ሰነድ መሠረት ይወሰናል፡፡ ግብር ከፋዩ ለግብር አወሳሰን ያቀረበው መረጃ ከተጣራ /ከተመረመረ/ በኋላ በመዝገቡ መሠረት ሊከፈል የሚገባው ግብር ይወሰናል፡፡

. በግምት የሚደረግ ውሳኔ

ማንኛውም ግብር ከፋይ በታክስ ሕግ መሠረት በማንኛውም የታክስ ጊዜ ማቅረብ የሚገባውን የታክስ ማስታወቂያ  ያላቀረበ  እንደሆነ ባለሥልጣኑ  በማንኛውም ጊዜ የሚያገኘውን ማስረጃ መሠረት በማድረግ ለታክስ ጊዜው  ታክስ ከፋዩ ሊከፍል የሚገባውን ታክስ በግምት (“የግምት ስሌት” ተብሎ የሚጠራ) ማስላት የሚችል ሲሆን የግምት ስሌቱ የሚከተሉትን  ይመለከታል፦

ሀ) በፌደራል  የገቢ  ግብር  አዋጅ  ሠንጠረዥ  “ለ”  ወይም“ሐ”  ኪሳራን  በሚመለከት  የታክስ ጊዜውን  የኪሳራ መጠን፤

ለ) በተጨማሪ  እሴት  ታክስ  አዋጅ  መሠረት  በግብዓት ላይ  በብልጫ  የተከፈለ  የተጨማሪ  እሴት  ታክስን በሚመለከት  ለታክስ  ጊዜው  በግብዓት  ላይ  በብልጫ የተከፈለውን  የታክስ  መጠን፤

ሐ)በሌላ ማንኛውም  ሁኔታ ዜሮ መጠንን ጨምሮ በታክስ ጊዜው ሊከፈል የሚገባውን የታክስ መጠን፡፡

1.1.  ግብር በግምት የሚወሰንበት ስልት ቀጥሎ ከተመለከቱት በአንዱ ይሆናል

የእለት ገቢን በመገመት /Estimated Assessment/ ፡-  የግብር ከፋዮችን የንግድ እንቅስቃሴ መሠረት ያደረገ በገቢ መርማሪዎች የህሊና ዳኝነት ላይ ተመስርቶ የቀን ገቢ ይገመታል፡፡ይህም የቀን ገቢ ግምት ወደ አማካኝ ዓመታዊ ገቢ መቀየር ለዚህ በተዘጋጀው ትርፋማነት ምጣኔ /Profitability rate/ ተለይቶ ባለው የገቢ ማስከፈያ ተመን መሠረት ግብሩ ይጠየቃል፡፡

በመረጃ መሠረት የሚወሰን፡- የግብር ከፋዩ መዝገብ ከሂሳብ አያያዝ ስርዓትና ከግብር ሕጉ አኳያ ተመርምሮ ተቀባይነት ሳያገኝ ሲቀር ከሶስተኛ ወገን በሚገኝ የግዥ ወይምየሽያጭመረጃ ላይ በመመሥረት ግብሩ ይወሰናል፡፡

በቁርጥ የሚወሰን ግብር /Presumptive Taxation/:- ግብር ከፋዮች መዝገብ ሳይዙ ሲቀሩ ወይም መዝገቡ ተመርምሮ ውድቅ ሲሆን ወይም መዝገብ የመያዝ የሕግ ግዴታ የሌለባቸው የደረጃ "ሐ" ግብር ከፋዮች ግብር ወይም ስለግብር ከፋዩ በቀን ገቢ ግምት ወይም ከሶስተኛ ወገን መረጃ ማግኘት ሳይቻል ሲቀር ግብሩ በቁርጥ /Presumptive/ ይወስናል፡፡

1.2.  ግብር አሰባሰብ

በሕገ መንግስቱ አንቀጽ 96 መሰረት ባለሥልጣን መ/ቤቱን ለማቋቋም ሐምሌ7/2000 ዓ.ም በወጣው አዋጅ ቁጥር 587/2000 አንቀጽ 6 ተራ ቁጥር 17 በተሰጠው ስልጣን መሠረት መ/ቤቱ ልዩ ልዩ የግብር/የታክሰ አይነቶችን በመወሰንና በመሰብሰብ ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህም፡-­

በወጪና ገቢ እቃዎች ላይ የሚጣል የጉምሩክ ቀረጥ፣ ታክስና ሌሎች ክፍያዎች፣ በፌዴራል መንግስት ባለቤትነት ስር ከሆኑ የልማት ድርጅቶች ላይ የሚሰበሰብ የንግድ ትርፍ ግብር፣ የስራ ግብር፣ የተጨማሪ እሴት ታክስና የአክሳይዝ ታክስ፣ ከብሔራዊ ሎተሪ እና ሌሎች የእድል ሙከራ ገቢዎች ላይ የሚሰበሰብ ታክስ፣ ከአየር፣ ከባቡርና ከባህር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የሚሰበሰብ ታክስ፣ በፌደራል መንግስት ባለቤትነት ስር ከሚገኙ ቤቶችና ሌሎች ንብረቶች ገቢ ላይ የሚሰበሰብ ግብር፣ የሞኖፖል ታክስ፣ የፌደራል የቴምብር ሽያጭና ቀረጥ ናቸው፡፡

1.3.  የግብር ምርመራ

ማንኛውም የተፈጥሮ ወይም የሕግ ሰው ባገኘው ገቢ ላይ በግብር ህጎች መሠረት የሚፈለግበትን ታክስ ሙሉ በሙሉ ስለመክፈሉ በግብር ከፋዩ እና ከሶስተኛ ወገን ከተገኙ መረጃዎች በመነሳት የሂሳብ የመግለጫዎችን በመመልከት ሰነዶችን የመመርመርና የማረጋገጥ ሂደት ነው፡፡

የግብር ምርመራ በዴስክ ኦዲት/Desk Audit/፣ በመስክ ኦዲት/Field Audit/፣ በውስን ምርመራ/Spot Audit/ እና አጠቃላይ የግብር መርመራ/Comprehensive General Audit/ ይከናወናል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም አልፎ አልፎ በግብር ከፋዩ በቀረቡ የሂሳብ መግለጫዎች የሰፈሩ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ የታክስ ጠቀሜታቸው /ተጽዕኖአቸው/ አነስተኛ በሚሆንበት ጊዜ የፅሁፍ ምርመራ /Mail Audit/ ሊደረግ ይችላል፡፡

 

Visitors: Yesterday 6 | This week 1 | This month 2203 | Total 824986

We have 332 guests and no members online