አማካይ የቀን ገቢ ግምት

Posted in Know How

በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀፅ 3 መሰረት የግብር ከፋዮች ደረጃ ቀድሞ ከነበረው ከፍ ብሏል፡፡ ደረጃ‹‹ሀ›› ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው 1 ሚሊዮን እና በላይ፣ ደረጃ‹‹ለ›› ድርጅቶችን ሳይጨምር ጠቅላላ ዓመታዊ ገቢያቸው ከ5 መቶ ሺ እስከ  1 ሚሊዮን ሲሆኑ ደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ደግሞ ድርጅቶችን ሳይጨምር ዓመታዊ ጠቅላላ ገቢያቸው ከብር 5 መቶ ሺ በታች ናቸው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ የሚገኙ ግብር ከፋዮች ላይ የሚታየውን የግብር አሰባሰብ ስርዓት ለውጥ ለማምጣት አንድ ግብር ከፋይ ዕቃ ሸጦ ወይም አገልግሎት ሰጥቶ ያገኘውን ዕለታዊ ገቢ መሰረት ያደረገ ግብር አሰባሰብ ተከትሎ ወደ ስራ ለመግባት የኢትዮጵ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ዝግጅቱን አጠናቋል፡፡

በዚህም መሰረት በ2009 ዓ.ም የሃገሪቱን እና የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መሰረት ያደረገ አዲሱ የፌደራል የገቢ ግብር አዋጅ ያስቀመጣቸውንና በ2003 የቀን ገቢ ግምት መረጃ ጥናት ላይ የነበሩትን ክፍተቶች በማረም አማካይ የቀን ገቢ ግምቱ የታዩ ችግሮችን ለመሙላት የተዘጋጀ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግለሰብ ግብር ከፋዮች የሚስተናገዱበት በመሆኑና ከዚህም በፊደራል ገቢ ግብር አዋጅ መሰረት የደረጃ ‹‹ሐ››  ግብር ከፋዮች በአማካይ የቀን ገቢ መረጃ መሰረት የሚስተናገዱ በመሆናቸው አማካኝይ የቀን ገቢ ግምቱ መውጣቱ አስፈልጓል፡፡

በተጨማሪም አማካይ የቀን ገቢ ግምቱ በህጉ መሰረት ደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ የሌለባቸው በመሆናቸው የሚጠበቅባቸውን ግብር እና ታክስ በቁርጥ እንዲከፍሉ ስለሚያደረግ ይህን አሰራር ያስቀረ በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡

ከዚህ ቀደም የቀን ገቢ ግምት የነበራቸው እና ጥናቱ የተሰራላቸው ግብር ከፋዮች ውጤቱ ሲተገበር ለንግድ ትርፍ ግብር ብቻ የ2009 በጀት ግብር እንዲከፍሉ የሚደረግ ሲሆን ቀጥተኛ ያልሆነ ታክስ በተመለከተ አመቱን ሙሉ በቀድሞ የቀን ገቢ ግምት መሰረት እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ከሐምሌ 1/2009 ዓ.ም. ጀምሮ አዲሱ የቀን ገቢ ግምት ቀጥታ ላልሆኑ ታክሶች ተግባራዊ ይሆናል፡፡

ነገር ግን ከዚህ ቀደም ግምት ያልነበራቸውና በታሳቢም ያልከፈሉ ግብር ከፋዮች ሆነው አሁንም መረጃ ያልተሰበሰበላቸውን በተመለከተ ከተቻለ ለማሳወቅ ሲመጡ ግምት እንዲቀርብ በማድረግ ይህ ካልሆነ በግብር ማስታወቂያ ወቅት እንዲቀርብ በማድረግ ለንግድ ትርፍ ብቻ የ2009 በጀት ዓመትን እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶችን በተመለከተ የዓመቱ ሙሉ ወይም ስራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ ራሳቸው በሚያሳውቁት እንዲከፍሉ የተደረገ ሲሆን ከሐምሌ 1/2009 ዓ.ም ጀምሮ አዲሱ የቀን ገቢ ግብር ቀጥታ ላልሆኑ ታክሶችም ተግባራዊ ይሆናል፡፡

 

Visitors: Yesterday 6 | This week 1 | This month 2203 | Total 824986

We have 336 guests and no members online