ሚዛናዊ እንሁን!

Posted in Know How

ሀገራችን የዘመናት ድህነትን ለማራገፍ እየጣረች ያለችበት ወቅት ላይ ትገኛለች። ይህንም ለማሳካት መንግስት ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ከፍተኛ ርብርብ ሲያደርግ መቆየቱና አሁንም በዚሁ ርብርቦሽ ውስጥ እንደሚገኝ ይታወቃል። በሁሉም ዘርፎች በተደረጉ ጥረቶች በአሁኑ ወቅት ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከታታይነት ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ጥቂት ሀገሮች አንዷ ለመሆን ችላለች። ይህን ልማት በዘላቂነት ለማስቀጠልና የድህነት ታሪካችንን ለማስቀየር መንግስት ለልማቱ ማስፈጸሚያ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ ያስፈልገዋል። ባለፉት ዓመታት ለፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ የሚውል ገንዘብ በብድርና ርዳታ ለማግኘት ጥረት ሲደረግና በዚያው አግባብ የልማት እቅዶቻችን ሲፈጸሙ እንደነበር የሚታወቅ ጉዳይ ነው። ነገር ግን በብድርና ርዳታ እስከመቼም ልማት ማካሄድ የሚቻል አይሆንም፤ የሀገር ክብርንም ይነሳል። ስለዚህ በሂደት የራስን ወጪ በራስ አቅም መሸፈን ያስፈልጋታል። ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ ያስፈልጋል።

እንደኛ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች የመንግስት ዋንኛ የገቢ ምንጭ ከታክስ የሚገኝ ነው። ስለሆነም ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ሃብት ልክ ግብር መስብሰብ ያስፈልጋል። የንግዱ ማህበረሰብ እና አጠቃላይ ህዝቡ ደግሞ በኢኮኖሚው ውስጥ ተንቀሳቅሰው ባገኙት ገቢ ልክ ለመንግስት የገቢ ግብር መክፈል አለባቸው።

የሀገራችን ኢኮኖሚ እያመነጨ ያለው እና ከታክስ እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ይታወቃል። ስለዚህ ይህን በአጭር ጊዜ ማመጣጠን ባይቻልም ለማቀራረብ በየጊዜው በርካታ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። ከእነዚህ አንዱ ከሚያዚያ 17 እስከ ግንቦት 30/2009 ዓ.ም. የተካሄደው የቀን ገቢ ግምት ነው። ስራው አድካሚና በርካታ ቅሬታዎችን ያስከተለ ሲሆን መፍትሄ እየተሰጠ ይገኛል።

በግምት ስራው ከነጋዴዎች የተነሱ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ አንዳንድ የመንግስትና የግል መገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊ ያልሆኑና በህዝብ ላይ ብዥታን የሚፈጥሩ ዘገባዎችን በማሰራጨት አሉታዊ ሚና ሲጫወቱ ተስተውሏል። ይህ ደግሞ ከልማታዊ መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሚና ያፈነገጠ አካሄድ ነው። ለአብነትም ሐምሌ መጀመሪያ ላይ ከወጡት ጋዜጦች በአንደኛው ላይ የተዘገበውን እንመልከት

 

“… ሰሞኑን በተፈጠረው የታክስ ግርግር ሳቢያ በርካታ ክስተቶች ተስተናግደዋል፤ በየቀበሌው በድንጋጤ አቅላቸውን ስተው የሚዘረሩ ሰዎችም አይታጡም። በተጨባጭ ለማረጋገጥ ባይቻልም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በቀን ገቢ ግምት የሶስት ሺህ ብር ታክስ ተጥሎባቸው ከድንጋጤ ብዛት መጸዳጃ ቤት ውስጥ ሞተው መገኘታቸውን የአካባቢ ሰዎች ሲናገሩ መደመጡን…”

 

“… የገቢ ግምት የአካባቢውን እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነና በዓመት 450 ብር ሲከፍሉ የነበረው የታክስ መጠን በአዲሱ ተመን መሰረት ከፍተኛ ጭማሪ እንዲኖረው በመደረጉ መማረራቸውን…” የሚሉ ይገኙባቸዋል።

እንደሚታወቀው የቀን ገቢ ግምቱ የሀገሪቷን ኢኮኖሚ፣ የገንዘብ የመግዛት አቅምና የዋጋ ግሽበትን መሰረት አድርጎ የተካሄደ ሆኖ ሳለ ይህን ማድረግ ‘የታክስ ግርግር…’  እንደመፍጠር ተደርጎ መዘገብ አልነበረበትም። ‘… በየቀበሌው በድንጋጤ አቅላቸውን ስተው የሚዘረሩ ሰዎችም አይታጡም…’ በሚል የተገለጸው ግምታዊ ሃሳብም እንደ ትክክለኛ መረጃ በመገናኛ ብዙሃን መቅረቡ ህዝብ ‘እውነት’ ነው ብሎ እንዲያምንና አሉታዊ ድርጊቶች ውስጥ እንዲገባ  የሚያደርግ ነው።

ሌላው ‘ … በተጨባጭ ለማረጋገጥ ባይቻልም….’ በሚል መንደርደሪያ የቀረበው ሲሆን ይህም አንደኛ፤ ዘጋቢው ርግጠኛ ያልሆነበትን ነገር ይዞ ነው የቀረበው። ሁለተኛ፤ የሚያስጠይቅ ከሆነ ደግሞ ጋዜጣውን ከኃላፊነት ለማሸሽ ይህን ሐረግ የተጠቀመ ይመስላል። ዘጋቢው ይህን ከማድረግ ‘መረጃው ትክክል ነው’ ብሎ ካመነ እንደ ሞቱ የተገለጹትን ግለሰብ ማንነትና በርግጥ በተባለው ምክንያት ስለመሞታቸው ማረጋገጫ ይዞ መቅረብ ነበረበት። ይህ ባልሆነበት ሁኔታ እንዲህ አይነት መረጃ በጋዜጣ ለህዝብ ማስተላለፍ የጋዜጠኛውን የሙያ ደረጃና የጋዜጣውን ተአማኒነት ግምት ውስጥ የሚከተው ነው።

እንዲሁም ‘… የአካባቢውን እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ ያላስገባ…’ በሚል የተጠቀሰውም አግባብነት የሌለው ነው። ግምቱ የተሰራው የአካባቢውን የንግድ እንቅስቃሴ እና ሌሎች አመላካች መስፈርቶችን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። ለምሳሌ መርካቶ እና ቦሌ ቡልቡላ አካባቢዎች በተመሳሳይ ሁኔታ የቀን ገቢ ግምት ሊሰራላቸው አይችልም። ከዚህም ሌላ ‘… ከፍተኛ ጭማሪ… ’ በሚል የተገለጸውም ትክክል አይደለም። በወቅቱ የተሰራው የቀን ገቢ ግምት እንጂ ዓመታዊ ቁርጥ ግብር አልነበረም። ዓመታዊ ቁርጥ ግብሩ ገና ሳይሰራ ‘ከፍተኛ ጭማሪ’ብሎ ለመዘገብ ጊዜው አልነበረም።

እንደሚታወቀው በልማታዊናዴሞክራሲያዊ ስርዓት መንግስት በሰላም፣ በዴሞክራሲና በልማት ዙሪያ በሚያደርጋቸው ጥረቶች መገናኛ ብዙሃን የበኩላቸውን ሚና የሚጫወቱ ይሆናል። መገናኛ ብዙሃን ሰላም እንዲሰፍን፣ ዴሞክራሲ እንዲያብብ እና ልማቱ እንዲፋጠን ለህዝብ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የማሳወቅና የማስተማር ስራዎችን በመስራት ብሄራዊ መግባባት እንዲመጣ አይነተኛ ሚና የሚጫወቱ ተቋማት ናቸውና ቅኝታቸውን በዚህ ማስተካከል አለባቸው።

ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ መገናኛ ብዙሃን እየተሰራጩ ያሉ ዘገባዎች ግን መልእክታቸው በሀገር ላይ ሰላም እንዳይሰፍን፣ ዴሞክራሲ እንዳያብብና ልማቱ እንዳይፋጠን የሚያደርግ ነው። ህዝብን በሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ አቅጣጫ የሚቀርጽ ሳይሆን በተቃራኒው የተጀማመሩ የልማት እንቅስቃሴዎችን ሊገታ የሚችል፣ ታዳጊ ዴሞክራሲያችን ይበልጥ እንዲቀጭጭ የሚያደርግና የህዝብን ሰላም የሚያደፍርስ አንደምታ ሲይዝ አስተውለናል።

አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ሊወጡ የሚገባቸውን ሚና ወደጎን ትተው ‘ተፈጠሩ’ የተባሉ ነገሮችን ምክንያትና ውጤት ሳይመረምሩ ጥሬ መረጃዎችን ይዘው እንደወረደ በማራገብ ህዝብን ብዥታ ውስጥ ሲከቱ ተስተውለዋል። እከሌ ወይም እከሊት  ‘እንዲህ አለ’ ወይም ‘እንዲህ አለች’ የሚሉ የጋዜጠኝነት ስነምግባርና ደረጃን ግምት ውስጥ የሚከቱ፣ ለአሉባልታ የቀረቡ ዘገባዎችን ስራችን ብለው ማሰራጨት የተያያዙት ይመስላል። በተለይም “… በተጨባጭ ማረጋገጥ ባይቻልም …” በሚል መንደርደሪያ  ያልተረጋገጠና በአሉባልታ ደረጃ የተነገረ መረጃን ‘እውነት ነው’ ብሎ ማሰራጨት ተገቢ አይደለም። ከዚህም ሌላ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን በህዝብ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ፣ የባለሙያዎቹን ስነ ምግባርና የሙያ ደረጃ ዝቅ የሚያደርጉና የህዝብ አመኔታን የሚያሳጡ የተሳሳቱ ዘገባዎችን ማውጣት በምንም መልኩ ለሀገር ማሰብ አይሆንም።

በህትመትም ይሁን በማንኛውም ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ብዙሃን የሚሰራጩ ዘገባዎች እውነታ የማያጠራጥርና ሚዛናዊ መሆን የሚገባው ሆኖ ሳለ  ጥሬ መረጃ ስለተገኘ ብቻ ለህዝብ መልቀቅ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። እንደነዚህ አይነት መረጃዎች በሀገር፣ በህዝብና በመንግስት አስተዳደር ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ቀላል አይደለም። ከዚህም ሌላ አንዳንድ ጋዜጦች ‘ተከሰቱ’ በሚሏቸው ችግሮች ዙሪያ በአምዶቻቸው የህዝብ፣ የምሁራንና የተቃዋሚ ፓርቲ አስተያየቶችን አስተናግደው ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸውን የገቢ ሰብሳቢ ባለስልጣን ወይም ሌሎች አካላትን አስተያየት ጠይቆ አለማካተትና ዘገባው ሚዛናዊ እንዲሆን አለማድረግ በራሱ ከሙያው ስነምግባር ያፈነገጠ ከመሆኑም ሌላ ምክንያቱ ራሱ ምን እንደሆነ ግራ የሚያጋባ ነው።

ስለሆነም ሜዲያዎች ከቀን ገቢ ግምቱ ጋር ተያይዞ የሚያሰራጯቸውን ዘገባዎች ይዘት ቆም ብለው ሊያጤኑት ይገባል። የሚያወጧቸው ዘገባዎች ሚዛናዊነትም ሊጠበቅ ይገባል። አሉባልታ የሚመስሉ፣ የህዝብን ስሜት የሚያዛቡ፣ ህዝብና መንግስትን የሚያጣሉ፣ ሀገራችን የተያያዘቸውን የልማት፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ጎዳና የሚያቀጭጩ ዘገባዎችን ማሰራጨት ለሀገር የሚበጅ አይሆንም። 

ይህ ሲባልለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በመስራት ላይ ክፍተቶች አልነበሩም ማለት አይደለም። እንደሚታወቀው አብዛኛው የንግዱ ማህበረሰብ ገቢውን በትክክል በማሳወቅ ታክስ የመክፈል ልምዱ አናሳ ነው። ታክስ በትክክል ከሚከፍሉት መካከልም ጥቂት የማይባሉት ለምን እንደሚከፍሉ ብዙም አልገባቸውም። ከዚህም ሌላ በታክስ ስርዓቱ ውስጥ ያልታቀፉ፣ እስከ ጭራሹም ታክስ ከፍለው የማያውቁና በህጋዊው ነጋዴ ላይ ጫና ሲፈጥሩ የቆዩ 8ሺ 651ያለንግድ ፈቃድ ሲነግዱ የተደረሰባቸው ነጋዴዎች  በዚህ ሂደት ወደ ታክስ መረቡ እንዲገቡ መደረጉ ሊታወቅ ይገባል። እንዲሁም አብዛኛው ህዝባችን የታክስ አስፈላጊነትና የውዴታ ግዴታ መሆኑ ላይ ግንዛቤው አነስተኛ ነው። ስለሆነም አስቀድሞ ለንግዱ ማህበረሰብና ለአጠቃላይ ህዝባችን ሰፋ ያሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን መስራት አስፈላጊ ነው። ለዚህ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ሚናቸውን ሊወጡ ይገባ ነበር። እዚህ ላይ፣ “ይህ ስራ በገቢ ሰብሳቢ ባለስልጣኑ አቅም መሰራት ነበረበት” የሚል ክርክር ሊነሳ ይችላል። ነገር ግን ጉዳዩ የሀገር ልማት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አጀንዳ ነው። ስለሆነም የሁሉም መገናኛ ብዙሃን አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን። ከዚህ አንጻር ተቋማቱ በቀጣይ አዎንታዊ ሚናቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን ግብር መክፈል የአገር ኩራት መሆኑንና የዜጎች መብትና ግዴታምጭምር እንደሆነ በሚያሰራጯቸው ዘገባዎችና ፕሮግራሞች ለህዝብ ሊያስጨብጡና ሊያስተምሩ ይገባል። የሀገሪቷ ኢኮኖሚ በሚያመነጨው ሀብት ልክ መንግስት ታክስ መሰብሰብ እንደሚገባው፤ ዜጎችም በኢኮኖሚው ውስጥ ተንቀሳቅሰው ባገኙት ገቢ ልክ ታክስ መክፈል እንዳለባቸው፤ ይህም የውዴታ ግዴታ እንደሆነ አውቀው ማሳወቅ አለባቸው። ለማሳወቅ ከሚያደርጉት ሩጫ ባሻገር አስቀድመው ስለቀን ገቢ ግምቱ የትርፍ ግብር መጠን፣ ስለ ግብር ማስከፈያ ስሌትና የንግድ ድርጅቶቹ በዓመት ይሰራሉ ተብሎ ስለተያዘው ቀን ጭምር መገንዘብ ይጠበቅባቸዋል። አንዳንድ ነጋዴዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተሳሳተ ቅሬታ ሲያቀርቡ የባለስልጣን መ/ቤቱን ኃላፊዎች ማነጋገርና መልስ እንዲያገኙ ማድረግም ይገባል። በአጠቃላይ መገናኛ ብዙሃን የጋዜጠኝነት ስነ ምግባርን በመላበስ እና በሚያቀርባቸው ዘገባዎች የተሟላ ግንዛቤ ይዘው ሚዛናዊ ዘገባ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

 

Visitors: Yesterday 6 | This week 0 | This month 2202 | Total 824985

We have 325 guests and no members online