በገቢዎች ሚኒሰቴር እና በባንኮች መካከል ያለ ቅንጅታዊ አሰራር ክፍተት የገቢ አሰባበሰቡ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ ይገኛል፡፡

Posted in Latest News


የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አደነች አቤቤ፣ የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቀበታ ፣ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸዉ የባንክ አመራሮች ህዳር 24/2011 ዓ.ም በዋናዉ መስሪያ ቤት ተገኝተዉ በጋራ ለመስራት በሚያስችሉ ነጥቦች ዙሪያ ዉይይት አካሄዱ፡፡

ኮንቴነሮች በደረቅ ወደብ የሚከማቹበት ምክንያት፣የዕቃዎች በወቅቱ አለመዉጣት የሚያሳድረዉ ተጽዕኖ፣ከሰነዶች ጋር በተያያዘ በባንኮች በኩል መታየት ስላለባቸዉ ጉዳዮች፣ከዕዳ ማካካሻና ዋስትና፣ከመመሪያና አሰራር አንጻር፣የአገር ዉስጥ ገቢ በተመለከተ እና የገንዘብ ሚኒስቴር የአገልግሎት አሰጣጥ በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ የጉምሩከ ኮሚሽነሩ አቶ ደበሌ ቀበታ ለተሳታፊዎቹ የመነሻ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡በተነሱት ነጥቦችም የባንክ አመራሮች ግልጽ እንዲደረግላቸዉ የሚፈልጉትን ጥያቄ አንስተዉ ከሚንስቴሩ የስራ ሃላፊዎች ማብራራያ ተሰጥቶባቸዉ በቀጣይም አብረዉ በጋራ ሊሰሩ በሚገባቸዉ ነጥቦች ላይ ስምምነት ላይ ደርሰዋል፡፡

በአሁኑ ሰዓት በመልቲ ሞዳልና ዩኒ ሞዳል ከተለያዩ አገሮች ተጭነዉ ጅቡቲ ወደብ የተከማቹ ከ13ሺ በላይ ኮንቴነሮች፣በተለይ ደግሞ በአገር ዉስጥ በሞጆ ደረቅ ወደብ እንዲሁ ከ15ሺ በላይ ኮንቴነሮች ተከማችተዉ ይገኛሉ፡፡

ይህ ሁኔታ በገቢ አሰባሰብ እና በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እያሳደረ በመሆኑ አስመጪዎች፣አገልግሎት ሰጪ የመንግስት ተቋማት እና ባንኮች በቅንጅት በመስራት ችግሩን በአጭር ጊዜ መፍታት ይገባቸዋል በማለት ሚኒስትሯ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አሳስበዋል፡፡

ከገቢ ዕቃ ጋር በተያያዘ በጉምሩክ እና በባንኮች መካከል የሚስተዋሉ የአሰራር እና የቅንጅት ክፍተቶችን በመለየት ፈጥኖ ለመፍታት እንዲሁም በዋስትና በሚሰጥ የዱቤ አገልግሎት (differed payment) ተፈጻሚ ለማድረግ በባንኮችና ጉምሩክ መካከል ሊኖር ስለሚገባ ሃላፊነት ሁለቱ አካላት በዋናነት ዉይይት ያደረጉባቸዉ ነጥቦች ናቸዉ፡፡

በመጨረሻም እንደዚህ አይነት የዉይይት መድረክ ቀጣይነት እንደሚኖረዉ እና በዉይይቱ የተነሱ ስምምነት ላይ የተደረሰባቸዉ ነጥቦችም ስራ ላይ ስለመዋላቸዉ ከአንድ ወር በኋላ በድጋሚ ተገናኝተዉ እንደሚመክሩ ሚኒስትሯ አሳዉቀዋል፡፡
#በዮሐንስአዳሙ

Visitors: Yesterday 2 | This week 102 | This month 1486 | Total 459629

We have 728 guests and no members online