በቦሌ ኤርፖርት ጉሙሩክ ቅንጅታዊ አሰራሩ መጠናከር እንዳለበት ተገለፀ፡፡

Posted in Latest News

የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክን ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት በመስራት ህገወጥነትን መከላከል እንደሚገባቸው ገለፁ፡፡

ሚኒስትሯ በጉብኝታቸው የገቢ ዕቃዎች መፈተሻ ቦታ፣ የግል መገልገያ ዕቃዎች መጋዘን እና የቦሌ ኤርፖርት መንገደኞች ጓዝን ጨምሮ ሌሎች የስራ ክፍሎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡ በተለይም በግል መገልገያ ዕቃዎች መጋዘን በመገኘት ከፍተሻ ሰራተኞች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም የፍተሻ ስራተኞቹ በስራው ላይ ክፍተት ፈጥረዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ለክብርት ሚኒስትሯ ገልፀዋል፡፡

ከእነዚህም መካከል ወጥ የሆነ የአሰራር ስርዓት አለመኖር፣የፍተሻ ስርዓቱ ደካማ መሆንና ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ አለመደገፍ ከባለሙያዎቹ እንደ ክፍተት የተነሱ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ክብርት ሚኒስትሯም ያሉ የህግ ማስከበር ክፍተቶች ጊዜ ሳይሰጣቸው መቀረፍ እንዳለባቸው አሳስበው ባለሙያዎቹ ስራቸውን በንቃትና በትጋት እንዲሰሩ ጠይቀዋል፡፡በቀጣይም ቅንጅታዊ አሰራርን ለማስፈን እና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ የማሻሻያ ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል፡፡

ሚኒስትሯ በተጨማሪም የቦሌ አየር መንገድ የመንገደኞች ጓዝን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸው ወቅትም የቦሌ ኤርፖርት የመንገደኞችና የካርጎ አገልግሎት አሰጣጥ በተናበበ መልኩ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ አገልግሎት አሰጣጡ ዘመናዊ እና ቀልጣፋ ለማድረግም ቅንጅታዊ አሰራር ወሳኝ እንደሆነ ከአመራሩ እና ሌሎች የስራ ክፍል ሀላፊዎች ጋር በነበራቸው ውይይት ገልፀዋል፡፡

ከሰሞኑ በአየር መንገዱ ሰራተኛ አቀባይነት እና በበረራ አስተናጋጅ ተቀባይነት በህገወጥ መንገድ ወደ ቻይና ሊወጣ የነበረ የተለያዩ ሀገራት የብር ኖቶች በቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅ/ፅ/ቤትና በብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞች መያዙ የሚታወስ ሲሆን ክብርት ሚኒስትሯም በጉብኝቱ ወቅት በቦታው በመገኘት ህገወጥ ገንዘቡ በምን መልኩ ሊያዝ እንደቻለ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል፡፡

ክብርት ሚኒስትሯ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት ህገወጥ ገንዘቡን በቁጥጥር ስር በማዋሉ ረገድ ጉልህ ሚና የተጫወቱትን የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሰራተኞችንና የቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅ/ፅ/ቤት ሰራተኞችን አመስግነዋል፡፡ በቀጣይም ይህ አይነቱ ትብብር ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባውና ለዚህም ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ ይገባል ብለዋል፡፡ እንዲህ አይነት ህገወጥ ድርጊቶች የአየር መንገዱን አለምአቀፍ ተቀባይነት እና ስም የሚያጎድፍ በመሆኑ በተሻለ ንቃት የቁጥጥር ስራው መጠናከር ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ሚኒስቴር መ/ቤቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአሰራር ማሻሻያዎችን በማድረግ ወደ ስራ እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

በጉብኝቱ ላይ በሚኒስቴር መ/ቤቱ የተቋማዊ አቅም ግንባታና ድጋፍ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታን ጨምሮ ሌሎች የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
#በሰኢድገልገሉ

Visitors: Yesterday 113 | This week 114 | This month 1290 | Total 448649

We have 486 guests and no members online