ነዳጅ ጭነዉ ወደ ሀገር ገብተው ሊወጡ የነበሩ ተሸከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

Posted in Latest News


ነዳጅ የጫኑ ሁለት ቦቴ መኪኖች መነሻቸዉን ጅቡቲ በማድረግ ወደ ሀገር ዉስጥ ገብተው ሊወጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር ዉለዋል፡፡ ተሸከርካሪዎቹ ነዳጁን ወደ አዶላ እና ደባርቅ እንዲያደርሱ የተሰጣቸውን ፍቃድ በመጣስ ተመልሰው ከሀገር ሊወጡ ሲሉ ተይዘዋል፡፡

ኮድ 95687/29557 ኢት የሆነ 46ሺ 700 ሊትር ነዳጅ የጫነ ተሽከርካሪ ወደ ደባርቅ እንዲሁም ኮድ 95829/29334 ኢት ተሳቢ ደግሞ 47ሺ59 ሊትር ነዳጅ ጭኖ ወደ አዶላ ከተፈቀደላቸው መስመር ውጪ ከሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ አቶ ሳሙኤል ሰላም እና አቶ ግዳይ ገ/ስላሴ የተባሉ አሽከርካሪዎች በገቢዎች ሚኒስቴር የጉምሩክ ኮሚሽን የጅግጅጋ ቅ/ጽ/ቤት ከአዲስ አበባ በደረሰዉ ጥቆማ መሰረት የጉምሩክ ሰራተኞችን ከክልሉ አድማ ብተና ጋር በማቀናጀት ሁለቱንም ተሸከርካሪዎች ጅግጅጋ ከመድረሳቸዉ በፊት ካራማራ በተባለ ቦታ ታህሳስ 15/2011 ዓ.ም ከቀኑ 6፡30 አካባቢ በቁጥጥር ስር መዋላቸዉን የቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ ስራ አስኪያጅ አቶ ደመላሽ ተሾመ አሳዉቀዋል፡፡

ይሄን መሰል ህገ-ወጥ ደርጊት ለመከላከል መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ ጠንክሮ እየሠራ እንደሚገኝ አቶ ደመላሽ ተናግረዉ ህዝቡም እያደረገ ላለዉ ንቁ ተሳትፎ ምስጋናቸዉን ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ ህገወጦችን በንቃት በመከታተል ለህግ እንዲቀርቡ በማድረግ የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም ስራ አስኪያጁ አሳስበዋል፡፡
#በዮሃንስአዳሙ

Visitors: Yesterday 2 | This week 81 | This month 1465 | Total 459608

We have 917 guests and no members online