አማካይ የቀን ገቢ ግምት ውጤት ይፋ ሊደረግ ነው፡፡

Posted in Latest News

User Rating: 0 / 5

Star inactiveStar inactiveStar inactiveStar inactiveStar inactive
 

ለመጨረሻ ጊዜ የቀን ገቢ መረጃ የማሰባሰብ ሥራ የተከናወነው በ2003 ዓ.ም ሲሆን በወቅቱ በግብር ስርዓቱ ያልታቀፉ ነጋዴዎች ወደ ስርዓቱ እንዲካተቱ አግዟል፡፡ በየሶስት ዓመቱ የንግድ ድርጅቶችን መረጃ ወቅታዊ የማድረግና ደረጃቸውን የመወሰን ሥራ መስራት የሚጠበቅ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል፡፡

በዚህ በጀት ዓመትም ወቅታዊ መረጃና ደረጃ ለመወሰን ከሚያዚያ 18/2009 እስከ ግንቦት 30/2009 ድረስ መረጃ የማሰባሰብና የቀን ገቢ ስሌት ተሰርቷል፡፡ ውጤቱም በቀጣይ ጥቂት ቀናት ውስጥ ለየግለሰቦች የሚገለጽ ይሆናል፡፡

ጥናቱን ተግባራዊ ለማድረግ በዝግጅት ምዕራፍ በአዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ 979/2008 አንቀጽ 3 መሰረት የተደረገውን የደረጃ እና የግብር ማስከፈያ የገቢ ማዕቀፍ ለውጥ፣የወቅቱ የገንዘብ የመግዛት አቅም እና በአገራችን በተጨባጭ የተፈጠረውን ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ግምት ውስጥ ያስገባ የቀን ገቢ መረጃ አሰባሰብ ሥራ መስራት የሚያስችል የስልጠና ሰነድ የማዘጋጀት፣ ከንግድ፣ ከፋይናንስና ከገቢዎች የተውጣጣ መረጃ አሰባሳቢ ኮሚቴ የማቋቋም፣ በየደረጃው፣ በየአደረጃጀቱና በየሚዲያው የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ወደ ግብር ስርዓቱ ያልገቡ ነጋዴዎችን ወደ ስርዓቱ ለማስገባት፣ የደረጃና ንግድ ለውጥ ያደረጉትን ትክክለኛ ደረጃ እንዲያገኙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጥቅም አለው፡፡

የተጠናው አማካይ የቀን ገቢ ግምት ይፋ ከመደረጉ በፊት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በመረጃ አሰባሰቡ ሂደት ወቅት ስለነበሩ ክፍተቶችና ጥንካሬዎች መግባባት በማስፈለጉ ከተወካዮቻቸው ጋር ውይይት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በ 6/10/2009 በኔክሰስ ሆቴል የተካፌደው መድረክ አንዱ ማሳያ ነው፡፡

በመድረኩ አጠቃላይ የአማካይ ገቢ ግምት ስራው ሪፖርት ቀርቦ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ በመረጃ ማሰባሰብ ወቅት የታዩ እቃ ማሸሽ፣ መረጃ መደበቅ፣ መረጃ ሊሰጥ የማይችል ሰው ማስቀመጥ፣ የንግድ ቦታን ዘግቶ መጥፋትና መሰል ችግሮች እንገጠሙ ተገልፃል፡፡  ቢሆንም ግን ለግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በተለያዩ መድረኮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በመስራት፣ ከመረጃ ማሰባሰብ ሂደቱ በፊት የተያዘን መረጃ በመጠቀምና በተቋቋሙት የኢንሲፔክሽን ቡድኖች ዳግም ምልከታ በማድረግ ጥናቱን ለማጠቃለል ተሞክሯል፡፡ ነገር ግን እስከአሁን ድረስ የንግድ ቦታቸውን ዘግተው የተሰወሩ ግብር ከፋዮች ተቋሙ ወደ ሌላ እርምጃ ከመሸጋገሩ በፊት ለጥናቱ በመተባበር እንዲያስገምቱ ጥሪው ቀርቧል፡፡

ለመሆኑ አማከይ የቀን ገቢ ግመት ጥናት

አላማዎች ምንድን ናቸው ?  

- ከተማአቀፍ የሆነ ተአማኒነት ያለው ፍትሀዊና ለቅሬታ ተጋላጭ ያልሆነ አማካኝ የቀን ገቢ ጥናት ከማከናወን የታክሱን ፍትሀዊነት ማረጋገጥ ነው፡፡

- የግምቱ ሥራ አጠቃላይ አገራዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የወቅቱን የገንዘብ  አቅም፣ የአዲሱን የገቢ ግብርና የታክስ አስተዳደር አዋጆችን መሠረት ያደረገ ተጨባጭ ጥናት በማካሄድ የግብር ከፋዮች ትክክለኛ ደረጃና እንደየደረጃቸው የሚጠበቅባቸውን ግዴታ አውቀው ከወዲሁ ዝግጁ እንዲሆኑ ማስቻል ነው፡፡

- የገቢ አቅምን መሠረት ያደረገ የቀን ገቢ ግምት ጥናት በማካሄድ የሕግ ተገዥነትን ማሣደግ እና የከተማውን የገቢ አሰባሰብ ለማጠናከር የሚያስችል አቅም መፍጠር ነው፡፡

አማካይ የቀን ገቢ ግምቱ

ጥናት ውጤት እንዴት ይተገበራል?

- በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/94 አንቀፅ 16 ታክስ የሚከፈልበት የንግድ ስራ እንቅስቃሴ የሚያከናውን ሆኖ ለተጨማሪ እሴት ታክስ ያልተመዘገበ ማንኛውም ሰው በማንኛውም የ12 ወራት ጊዜ ውስጥ ያከናወነውን ታክስ የሚከፈልበት ግብይት ከብር 500 ሺ በላይ ወይም የዘርፍ ተመዝጋቢ ከሆነ እንዲሁም የተርን ኦቨር ታክስ የሚጣለው ሽያጭ ላይ ቢሆንም የግብር ከፋዩ ጫና ለመቀነስ ለሽግግር ጊዜው ብቻ ከዚህ በታች በተጠቀሰው አግባብ አማካይ የቀን ገቢ ግምት ጥናት ውጤት ተግባራዊ ይሆናል፡፡

- የቀድሞ የቀን ገቢ ግምት የነበራቸው፤ የ2009 አማካይ የቀን ገቢ ግምት ጥናት የተሰራላቸው ግብር ከፋዮች ውጤት ሲተገበር ለንግድ ትርፍ ግብር ብቻ የዓመቱ ማለትም የ2009 ሙሉ በጀት ዓመት ግብር ኢንዲከፍሉ የሚደረግ ሲሆን ቀጥታ ያልሆነ ታክስ በተመለከተ የተጨማሪ እሴት ታክስ፤ የተርን ኦቨር ታክስ እና የኤክሳይዝ ታክስ የአመቱን በቀድሞው የቀን ገቢ ግምት መሠረት እንዲከፍሉ ይደረጋል፡፡ ከሀምሌ 1/2009 ዓ.ም ጀምሮ አዲሱ የቀን ገቢ ግምት ቀጥታ ላልሆኑ ታክሶችም ተግባራዊ ይሆናል፡፡ የተጨማሪ እሴት ታክስ የመመዝገብ ግዴታ በህግ የተጣለባቸው ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ተመዝጋቢ ይሆናል፡፡

- ከሁን ቀደም የቀን ገቢ ግምት ተገምቶላቸው የማያውቁና በታሳቢ ግብር/ታክስ ሲከፍሉ የነበሩ ግብር ከፋዮች በአዲሱ ግምት መሰረት እስከ 2009 በጀት ዓመት ወይም ስራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ የንግድ ትርፍ ግብር ብቻ እንዲከፍሉ የሚደረግ ሲሆን ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶችን ማለትም የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ የተርን ኦቨር ታክስ እና የኤክሳዝ ታክስ በተመለከተ ስራ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ በታሳቢ ሲከፍሉት በነበረው እንዲያልቅ ተደርጎ ከሐምሌ 1/2009 ጀምሮ በአዲሱ የቀን ገቢ ግምት የሚስተናገዱ ይሆናል፡፡

- ቀድሞ የቀን ገቢ ግምት ያላቸው ነገር ግን በተለያየ ምክንያት የ2009 በጀት ዓመት የቀን ገቢ ግምት ያልተሰራላቸው እና ከአሁን በፊት ግምት ያልነበራቸውና በታሳቢም ሳይከፍሉ የቀሩ፤ ግብርና ታክሳቸውን ለማሳወቅ ሲመጡ የሚገመትላቸው ወይም መረጃ የሚሰበሰብ ይሆናል፡፡ ይህ ክልተቻለ በቀድሞ ግምት መሰረት ግብርና ታክሱን እንዲያሳውቁ ተደርጎ ከግብር ማስታወቂያ በኋላ የቀን ገቢ ግምት እንዲቀርብ በማድረግ ለንግድ ትርፍ ግብር ብቻ የዓመቱ ማለትም የ2009 ሙሉ በጀት ዓመት በአዲሱ ግምት መሰረት የንግድ ትርፍ ግብር እንዲከፍሉ የሚደረግ ሲሆን ቀጥታ ያልሆኑ ታክሶችን በተመለከተ በቀድሞ የቀን ገቢ ግምት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን  የተጨማሪ እሴት ታክስ የመመዝገብ ግዴታ በህግ የተጣለባቸው ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ ተመዝጋቢ ይሆናሉ፡፡

 - መረጃው ከባለቤቶቹ ግብር ከፋዮች መሰብሰቡ ጥናቱን በተቻለ መጠን ፍትሃዊና ታማኝ ለማድረግ ስለሚረዳ ነው፡፡ ነገር ግን ትክክለኛና ተጨባጭ ቅሬታ አለኝ ለሚል ግብር ከፋይን የሚያስተናገዱ ቅሬታ ሰሚ ኮሚቴዎች በወረዳ እና በቅ/ጽ/ቤት ደረጃ ተቋቁመዋል፡፡

 - አማካይ የቀን ገቢ ግምት ጥናት ግብር ከፋዩን ወደተሻለና ፍትሃዊ የግብር ስርዓት ከማምጣቱ ባሻገር ህጋዊውን ነጋዴ ከገበያ ለማስወጣት የሚሯሯጡ ህገ ወጥ ነጋዴዎችን ወደ ስርዓቱ እንዲገቡ ካልሆነም እራሳቸው እንዲወጡ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት ስለሆነ ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ በእኔነት ስሜት እንዲተባበር ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ያሳስባል፡፡

በዳንኤል ታደሰ

Visitors: Yesterday 89 | This week 469 | This month 1665 | Total 819632

We have 372 guests and no members online